ፋና:

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) ኢትዮጵያ በሱዳን ወደብ በኩል የመልቲ ሞዳል ስርአትን ለመተግበር የሚያስችል ድርድር ከሱዳን ጋር እያደረገች ነው።

የኢትዮጵያ የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን የሚያስፈልገውን የስምምነት ሰነድ አዘጋጅቶ በመላክ የሱዳንን ምላሽ እየጠበኩ ነው ብሏል።

በ2007 ዓ.ም ስራ የጀመረው የፖርት ሱዳን ወደብ እስከ 15 በመቶ ያህሉን የሀገሪቱን የወጪ ገቢ ንግድ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ የታሰበ ነው።

በተለይም የሰሜኑን የሀገሪቱ ክፍል ተደራሽ በማድረጉ ረገደ ከወጪም ሆነ ከፍጠነት አንጻር የተሻለ መሆኑም ታምኖበታል።

ታዲያ በዚህ ደረጃ ጥቅም የሚያስገኘው ይህ ወደብ ከጥቂት የመንግስት ተቋማት በስተቀር የተጠቃሚው ቁጥርም ሆነ የመጠቀም አቅም ዝቅተኛ የሚባል መሆኑን ነው ከኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ የሚያሳየው።

በፖርት ሱዳን በኩል ለመጠቀም ከታቀደውም በሶስስ ዓመት ውስጥ 1 ነጥብ 2 በመቶ ያህሉን ብቻ ነው ማሳካት የተቻለው።

ስለዚህ ተጠቃሚውን ለማስፋት ተጨማሪ ስራ የሚያስፈልግ ሲሆን፥ በዚህ ላይ ዝርዝር ጥናት ከማጥናት በተጓዳኝ የተሻሉ አሰራሮችን መዘርጋት አንዱ እንደሆነ ታምኖበታል።

በባለስልጣኑ የሎጀስቲክ ማሰተባበሪያና ክትትል ዳይሬክተሩ አቶ ተመስገን ይሁኔ እንደሚሉት፥ የመልቲ ሞዳል ስርአትን መጠቀም የሚለው ትኩረት ተሰጥቶታል።

ለተግባራዊነቱም በኢተዮጵያ በኩል የስምምነት ሰነድ በዝርዝር ተዘጋጅቶ ለሱዳን ተልኮ ምላሹ እየተጠበቀ መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ የሚናገሩት።

ምላሹ በቅርቡ እንደሚመጣ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ለስምምነቱ ምክኒያታዊ ነጥቦች የተቀመጡ በመሆኑና ዝግጅቱን የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ይጠበቃል ብለዋል።

የስምምነት ሰነዱ ላይ ከማስተካከያ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮች ካሉም በዛ ደረጃ የሚታዩ መሆኑም ተገልጿል።

እስካሁን በጅምር ደረጃም ቢሆን፥ ወደቡን እየተጠቀሙ ካሉ ተቋማት የመልቲ ሞዳል ሰርአቱ ወደ ተግባር ከገባ ጠቃሚነት እንዳለው ያነሳሉ።

በፖርት ሱዳን በኩል የመልቲ ሞዳል ስዓት በስፋት ሲተገበር አሁን ከተገኘው ጥቅም በተሻለ ለማግኘት የሚያስችል እንደሚሆንም ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ በበኩሉ የመልቲ ሞዳል ስርአቱ ወደ ተግባር ሲገባ እቅዱን ለማሳካት ያስችላል ብሏል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን፥ በወደቡ ላይ የራስ ጽህፈት ቤት መክፈትና ወደ ተግባር ሲገባ አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ በደቡብ ጎንደር ደረቅ ወደብ መገባት የሚሉት ይገኙበታል።

ሌሎች ወደቡን ካለመጠቀም ጋር ተያይዞ ያሉ ክፍተቶችን በመለየት ተጨማሪ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ካስፈለጉ መዘረግት የሚለው ግን ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

በሀይለኢየሱስ ስዩም ፋና

Facebook Comments
Spread the love