ሰኔ 29፤2009

የሰሜን ብሄራዊ ፓርክን የአደጋ ስጋት ካለባቸው የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ማስወጣቱ በኢትዮጵያ ላሉ ሌሎች ፓርኮች ምሳሌ እንደሚሆን የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

መንግስት ፓርኩን ወደ ነበረበት ደረጃ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንና ጥረቱም ውጤት ማስገኘቱን የባህልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶክተር ሂሩ ወልደማርያም በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የፌደራል መንግስትና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጋራ ባደረጉት ርብርብ በፓርኩ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ለማስወጣትና ለተነሺዎች ምትክ ቦታ ለመስጠት 200 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ መደረጉንም ነው ሚስትሯ የገለፁት፡፡

ፓርኩ ወደ ቀድሞ ክብሩ እንዲመለስ ከፍተኛ ርብርብ ላደረጉ ባለድርሻ አካላትም ሚንስቴር መስሪያቤቱ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1970 በዩኔስኮ የአለም ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላለፉት 21 ዓመታት በአደጋ መዝገብ ውስጥ ከሚገኙ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ አንዱ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ፓርኩ በአደጋ መዝገብ ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ በፓርኩ ክልል የሰዎች ሰፈራ መስፋፋት፣ ፓርኩን አቋርጦ የሚያልፍ መንገድ መኖሩ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የፓርኩ ወሰን ክልል እየጠበበ መምጣቱ ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፡፡

በዚህም ምክንያት በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ እንስሳት ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንዲመናመኑ አድርጓቸው እንደነበረ ተመልክቷል፡፡

በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ እንደጭላዳ ዝንጀሮ፣ ዋልያና ቀይ ቀበሮዎች ያሉ ብርቅዬ የዱር እንስሳትን ጠብቆ በማቆየት ረገድ የተሰራው ስራ የሚደነቅ መሆኑንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ፓርኩ  አደጋ ስጋት ካለባቸው የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ማስወጣቱን አስመልክቶ  ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በናትናኤል ፀጋዬ   EBC

Facebook Comments
Spread the love